በ124 ዓመት የዓድዋ በአል ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ያስተላለፉት መልእክት

በ124 ዓመት የዓድዋ በአል ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ያስተላለፉት መልእክት
===============
ክብርት ፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ የኢፌዲሪ ፕሬዜዳንት

ክብርት ወ/ሮ ከርያ ኢብራሂም የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ

ክብርት ዶ/ር ሂሩት ካሳው የኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር

ክቡር ፕሮፌሰር ሃሪሶን ቪክተር የአፍሪካ ህብረት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኮሚሽነር

የተከበራችሁ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች

ክቡራን የሃይማኖት መሪዎች እና ኣባት አርበኞች እንዲሁም ከተለያዩ ኣካባቢዎች እዚህ በመሀከላችን የተገኛችሁና ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች
የተከበራችሁ የዓድዋና ኣካባቢዋ ነዋሪዎች
ክቡራትና ክቡራን

ከሁሉ በፊት ከተለያዩ አካባቢዎች ለመጣችሁም ሆነ በዓሉን ለማክበር ከአድዋና አካባቢዋ ለተሰባሰባቹህ ህዝቦች በራሴና በትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ስም እንኳን ለ124ኛው ዓመት የአድዋ የመላ ጥቁር ህዝቦች የነጻነት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን! ማለት እወዳለሁ።

በአድዋ የተሰራው አንፀባራቒ የድል ታሪክ የብዙ ትምህርቶች ምንጭ የሆነ፥ አገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም ኣቀፋዊ ፋይዳ ያለው ታሪካዊ ድል ነው። አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ለአገራቸው ክብር፣ ብሄራዊ ጥቅም፣ ህልውናና ልዕልና ማስከበርና ማስጠበቅ ግዴታና ኃላፊነት ያላቸው መሆኑን በመገንዘብ፤ ከፍተኛ ስልጠናና ዝግጅት ካለው የጣልያን ሰራዊት የማጠቃለያ ውግያ በአድዋ በመግጠም ጦርነቱን በማሸነፋቸው ደካም ተብለው የሚፈረጁ ህዝቦች ሳይለያዩ በጋራ ለጋራ ተራማጅ ህዝባዊ ኣላማ ከተነሱ ሊገመት፥ ሊተነበይ የማይችል ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉ አድዋ ህያው ምስክር ነች።

የአድዋ ድል ለውጭ ሃይል ተፅእኖና ጣልቃ ገብነት እንደማንበረከክ፥ ለነፃነታችን ሁሉንም ለመክፈል ወደኃላ የማንል ህዝቦች መሆናቸን ያሳያል። ከአድዋ የድል ታሪክ እንደምንረዳው የወራሪ ሠራዊት ጦር መሪ የነበረው ጄኔራል አልቤርቶኒ በኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ሲማረክ የሠራዊቱ ዋና አዛዥ ጄኔራል ባራቴሪ ከአጃቢዎቹና ከተበታተኑ የጣሊያን ወታደሮች ጋር የሀፍረት ሸማ ለብሶ ወደ መጣበት የተመለሰበት የዓለምን ህዝብ ያስደነገጠ ባላደጉ አገራት ይፈጸማል ተብሎ የማይታሰብ ድንቅ ድል ነው።

የአድዋ አርሶ አደር ኋላቀር ጥቂት መሳሪያዎችን፣ ጦርንና ጎራዴን ይዞ በርካታ መድፎችን፣ ብዙ ሺህ ቀላልና ከባድ መትረየሶችን፣ በርካታ የነፍስ ወከፍ ጠመንጃዎችን በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ መሰል ጥይቶቻቸው ጋር የማረከበትና አኩሪ ጀብዱ የፈጸመበት ቦታ ነው ፡፡

ከዚህ የምንወስደው ትምህርት ዘመናዊ መሳሪያ መታጠቅ አለመታጠቅ፣ የወታደር መብዛት ማነስ፣ መሰልጠን አለመሰልጠን የየራሳቸው አወንታዊና አሉታዊ ጫና ቢኖራቸውም ህዝባዊ አንድነት፣ እምነትና ጽናት ምንጊዜም የድል ባለቤት መሆኑን ነው። ለዚህ አኩሪ ድል ላበቁን እና የእብሪት ወረራውን ለመከቱ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ታላቅ ክብር ይገባቸዋል። ይህ አኩሪ ታሪካቸውም ምንግዜም እየተዘከረ የሚኖር ህያው ድል ነው።

በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደሚገለጸው አድዋ የኢትዮጵያ ክብር ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች ክብር የተገለጸበትና ነጻነት የተረጋገጠበት የድል በዓል ነው።

የዓድዋ ድል በተለይ በወቅቱ በቅኝ ግዛት ቀንበር ወድቀው ለነበሩት የአፍሪካ አገሮች እና በዘር መድልዎ ይሰቃዩ ለነበሩ ጥቁር ህዝቦች ተስፋን የፈነጠቀ የነፃነት አርማም ነበር።

ክብርት ፕሬዝዳንት
ክቡራትና ክቡራን
አሁን በአገራችን እየተከሰተ ያለውን የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነትና በብሄራዊ ማንነታችን፣ ብሄራዊ ክብራችንና ሉአላዊነታችን የተደቀነውን አደጋ ለማስተካከልም የአድዋ ጦርነት መንስኤ ከሆነው የውጫሌ ውል በአስተማሪነቱ ወስደን ልንጠቀምበት ይገባል። በቅርቡ በኢትዮጵያ ፖለቲካና በህዳሴ ግድብ ዙርያ በታላላቅ አገሮች ብቻ ሳይሆን በአላፊ አግዳሚውም እየታዩ ያሉ ጣልቃ ገብነቶች ከነመነሻ ምክንያታቸው ታውቀው ተገቢ ጥንቃቄ በመውሰድ ወቅታዊ፥ በሳልና የማያዳግም ምላሽ መስጠት ይገባል።

ሰሞኑ የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ የቀረበው የውል ሰነድ ቆም ብለን ከውጫሌ ውል በመማር በውሉ የሰፈሩ ሃሳቦችና ቃላቶች በሉአላዊነታችን ላይ የመጡ ከዛም አልፈው ለሌላ ጂኦፖለቲካ አላማ ማስፈፀሚያ ገፀ በረከትና እጅ መንሻ ሆኖ እንዳያገለግል በከፍተኛ ጥንቃቄና ሃላፊነት መፈፀም ይገባዋል። ወደ ጦርነት ካስገባን የውጫሌ ውል ሳንማር ቀርተን በአገር ላይ ጉዳት ቢደርስ ይህ ሌላ ስህተት ሳይሆን የሚያስጠይቅ ጥፋት መሆኑ አይቀርም።

የድሮ ቀኝ ገዥዎች የሚፈልጉትን አገር ወረው በጉልበት፥ በመሳርያ ይገዙ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን የአሁኑ ቀኝ ገዥዎች ግን አገሮች የፖሊሲ ነፃነት እንዳይኖራቸው በሪፎርም፥ በብድርና እርዳታ ስም ለእነሱ የሚጠቅም ለውጥ እንዲደረግ በመጫን በቁጥጥራቸው ስራ በማስገባት፥ ዜጋው በመሰለው አገሩን እንዳያስተዳድር የሚያደርጉ መሆኑ በመገንዘብ እኛም እንደ ቅድመ አያቶቻችንና አያቶቻችን አገራችን ከማንኛውም የውጭ ጣልቃገብነት ጠብቀን ነፃነታችን አስጠብቀን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ታሪካዊ ሃላፊነታችንና ግዴታችን መሆኑ መገንዘብ ይገባል።

ክብርት ፕሬዝዳንት
ክቡራትና ክቡራን
ይህ ዘመን ተሻጋሪ የሆነው የአድዋ ድል ታሪካችን ከኢትዮጵያውያን አልፎ የሁሉም የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ምልክት ሆኖ ሳለ በተገቢው ሁኔታ መጠናት፣ መጠበቅ፣ መተዋወቅ ይገባው ነበር፥ ይገባዋልም። ይህ አኩሪ ታሪካችን ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ፣ ዓድዋና አካባቢዋ በስፋት በማልማት እና ዋና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ ሊደረግ ይገባል፡፡

ቀደም ሲል የተጀመረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፓን አፍሪካን ዩኒቨርስቲ በአድዋ ለማቋቋም ተጨባጭ እንቅስቃሴ በመካሄድ ላይ ይገኛል። ይህ የፓን አፍሪካን ዩኒቨርስቲ በአገራችን ካሉት ዩኒቨርስቲዎች የተለየ በአድዋና በሌሎች የጥቁር ህዝቦች አኩሪ የታሪክ ገድል ዙርያ የሚካሄዱ ምርምሮችና ተዛማጅ ስራዎች ለተማራማሪዎች አገልግሎት የሚሰጥ ልዩ ዩኒቨርስቲ ነው። ይህ ልዩ ዩኒቨርስቲ በዓለም ያሉ ጥቁር ህዝቦችና ተራማጆች ትብብር የሚሰራ ቢሆንም እኛ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በተለይ ተባብረን በአንድነት ዩኒቨርስቲው መስራት ይጠበቅናል።

በመሆኑም የትግራይ ክልል የዩኒቨርስቲው የግንባታ ስራ እስከሚጠናቀቅ በገንዘብና በአይነት ድጋፍ ለመስጠት ቃል በገባው መሰረት የፓን ኣፍሪካን ዩኒቨርስቲ ፕሮጀክት ማስተር ፕላንና ዲዛይን ስራ በማስጀመር የማስተር ፕላኑ ስራ በማገባደድ ወዲ ዝርዝር ዲዛይን በመሸጋገር ላይ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች ዝግጅቶች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ። ይህ የአድዋ ታሪካችን በቱሪዝምና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ገፅታም ህዝባችን ተጠቃሚ ለማድረግ በቀጣይ አቅም በፈቀደ ዝርዝር ስራዎች ይካሄዳሉ። በዚህ ሁሉ ተግባራት እየተሳተፋችሁ ላላችሁ ሀገር ወዳድ ሙሁራን እና በየደረጃው እያስተባበራችሁ ላላቸሁ ልዩልዩ ኮሚቴዎች እና የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም በፕሮጀክቱ ማስተር ፕላንና ዲዛይን ስራ በሃላፊነት መንፈስ እየተሳተፋቹህ ያላቹህ ኩባንያዎች በራሴና በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ ሥም የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

የዓድዋን ድል ስናስብ መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ፣ አገር ተረካቢው ወጣቱ ትውልድ የቀደምት ጀግኖች አባቶቻችን ተጋድሎ በማስታወስ ሉኣላዊነታችንን ከማንኛውም የውጭ ጣልቃ ገብነት በመከላከል ሰላም በማስጠበቅ በፀረ -ድህነትና ህላ ቀርነት ትግሉ በተነሳሽነትና በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ለማሳሰብ እወዳለሁ። በመጨረሻም ይህ ታላቅ ክብረ በዓል በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር ላደረጉ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፤ የትግራይ ማእከላዊ ዞን አስተዳደር፣ የዓድዋ ከተማ አስተዳደርና ህዝብ ከፍተኛ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

ክብር ለሠማዕታት!!
የዓድዋ ድል የመላው ጥቁር ህዝቦች ድል ሆኖ ሲታወስ ይኖራል!!
አመሰግናለሁ፥

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *