“ከመጋረጃ በስተጀርባ በተፈበረከ ሐሰተኛ፣ የበሬ ወለደ ወሬ የሚደናገር ህዝብ ፈፅሞ ኣይኖርም”!

“ከመጋረጃ በስተጀርባ በተፈበረከ ሐሰተኛ፣ የበሬ ወለደ ወሬ የሚደናገር ህዝብ ፈፅሞ ኣይኖርም”!

ባለፉት ሁለት ዓመታት፣ የተቀነባበረ፣ ሓሰተኛ ዴኮሜንታሪ ፊልም ሰርቶ በማሰራጨት፣ በትግራይ ህዝብና መንግስት ላይ ሲሰነዘር የነበረው ብሄር ተኮር ጥቃት፣ ኣገርሽቶቦት፣ ትላንት ግንቦት 16/2012 ዓ/ም፣ በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት፣ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል፣ በብልፅግና ፓርቲ ፌስቡክ ፔጅ፣ በኣዲስ ኣበባ ብልፅግና ፓርቲ ፌስቡክ ፔጅ፣ በኣማራ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ከግል ሚዲያዎች፣ ማለትም በኢሳት፣ በኣባይ ሚዲያ፣ በዘሀበሻ ወዘተ የሚባሉ እንዲሁም መረጃ ዶት ኮም እና ኣዲስ ፋክት በተባሉ ማህበራዊ የሚዲያ ኣውታሮች የበሬ ወለደ ትርክታቸውን ኣሰራጭቷል፡፡እነዚህ በአንድ ሳምባ የሚተነፍሱ ሚዲያዎች በትግራይ ክልል የተለያዩ ኣከባቢዎች የፀጥታ መደፍረስ መፈጠሩ ተገለፀ፣ በተለያዩ ኣከባቢዎች ማለትም በሽረ እንዳስላሰ እና ኣከባቢዎች፣ እንዲሁም በዋጅራትና ኣከባቢው ሰለማዊ ሰልፎች ተካሄዱ፣ ፍትህ መጓደል ኣለ ወዘተ፣ ስለዚህ ይህ ችግር ወደ ከፋ ደረጀ ከመሸጋገሩ በፊት የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ ጠየቁ በማለት፣ እንዲሆንላቸው የሚመኙትን ቅዠት፣ ራሳቸው ፈብርከው ሐሰተኛ፣ የበሬ ወለደ ወሬ ኣሰራጭቷል፡፡

በኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት የሚተዳደሩት እነዚህ የሚበዙት ሚዲያዎች ትላንት ያሰራጩት ሐሰተኛ ወሬ ባለፉት ሁለት ዓመታት የፌዴራል መንግስት እያሰተዳደረ ላለው ኣካል እና ለእነዚህ የሚዲያ ኣውታሮች፣ ትልቅ ራስ ምታት የሆነባቸውን በትግራይ ህዝብና መንግስት ያለው እንደ ብረት የጠነከረ ግንኙነት፣ ክፍተት ይፈጥርልናል ብሎው፣ ትላንት ሐሰተኛ ወሬ ማሰራጨታቸው ከንቱ ልፋት ከመሆኑ በዘለለ “ከመጋረጃ በስተጀርባ በተፈበረከ ሐሰተኛ፣ የበሬ ወለደ ወሬ የሚደናገር ህዝብ ፈፅሞ ኣይኖርም”! ይልቁንም የእነዚህ ሚዲያዎች ኣጎብዳጅ ባህሪ ፍንቱው ኣርጎ በማሳየት እርቃናቸው ያስቀረ ቅሌት ውስጥ መግባታቸውን ነው፡፡

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል በየትኛውም ኣከባቢ፣ የተካሄደ ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ የተፈጠረ የሰላም መደፍረስና ግርግር ፈፅሞ ያልተሰማ እና መሬት ላይ የሌለ መሆኑን ለወዳጅም ለጠላትም ማሳወቅ እንወዳለን፡፡ እውነታውም ይሄው ነው፡፡

ስለዚህ፣ ሐሰተኛ ወሬ በማሰራጨት፣ የተጠመዱት እነዚህ ሚዲያዎች፣ በኣጠቃላይ በኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ላይ በየዕለቱ እያሳዩ ያሉት፣ ንቀትና ቧልት፣ እንዲሁም በትግራይ ህዝብና መንግስት ላይ እየሰነዘሩት ያሉት ብሄር ተኮር ጥቃት ኣደብ እንዲገዙ፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንም፣ ግንቦት 16/2012 ዓ/ም ከላይ ስማቸው በተጠቀሱት እና ለጊዜው ስማቸው ባልተጠቀሱት ሚዲያዎች የተሰራጨውን ሐሰተኛ የበሬ ወለደ ወሬ አጣርቶ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *